በርእደ መሬት ጉዳት ሥራ ያቆመው የከሰም ስኳር ፋብሪካ በርካታ ሠራተኞቹን ሊያሰናብት ነው

ዐፋር

በአፋር ክልል አዋሽ ፈንታሌ ወረዳ በተደጋጋሚ ባጋጠመው ርእደ መሬት የመፍረስ ጉዳት የደረሰበት የከሰም ስኳር ፋብሪካ፣ በሺሕ ለሚቆጠሩ ሠራተኞቹ የመጨረሻ የስንብት ማስታወቂያ አወጣ፡፡

የፋብሪካው ሠራተኞች ማኅበር ውሳኔውን "አግባብነት የሌለው" ሲል ተችቷል፡፡ "ፋብሪካው ለሠራተኞቹ የስንብት ማስታወቂያ ከማውጣቱ በፊት ሌሎች አማራጮችን መመልከት ነበረበት፤" ብሏል ማኅበሩ፡፡

የፋብሪካው ሠራተኞች በበኩላቸው፣ "በስንብት ማስታወቂያው ተደናግጠናል፡፡ ውሳኔው አኹን ያለውን የኑሮ ውድነት እና የጸጥታ ስጋት ግምት ውስጥ ያላስገባ ነው፤" ሲሉ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል፡፡

Your browser doesn’t support HTML5

በርእደ መሬት ጉዳት ሥራ ያቆመው የከሰም ስኳር ፋብሪካ በርካታ ሠራተኞቹን ሊያሰናብት ነው

የፋብሪካው አመራሮች፣ ውሳኔያቸውን አስመልክቶ እስከ አኹን ለብዙኃን መገናኛ የሰጡት መግለጫ የለም፡፡ የአሜሪካ ድምፅም ተደጋጋሚ ሙከራ አድርጎ አልተሳካለትም፡፡

የአገሪቱን የስኳር ፋብሪካዎች በበላይነት የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ፣ ፋብሪካው ሠራተኞቹን ለማስቀጠል በሚያስችል ቁመና ላይ አይደለም፤ ብሏል፡፡

የአገር አቀፍ እርሻ እና አግሮ ኢንዱስትሪ ሠራተኛ ማኅበራት ፌዴሬሽን ደግሞ፣ በሠራተኞቹ ላይ ስለደረሰው ጉዳት እና በመጻኢ ዕድላቸው ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋራ እየተወያየ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡